Thursday, October 1, 2009

ሤራ፤ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት

ሤራ፤ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት


ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ አንደኛ መጽሐፍ፤

ደራሲ፤ ወርቅ አፈራሁ ከበደ

ግምገማ፣ በስለሺ ጥላሁን

ደራሲው ከዚህ ቀደም እ ኤ አቆጣጠር 2006 ዓ ም በእንግሊዘኛ ቋንቋ “Borderless Love: An Ethiopian Eritrean Love
Story” በሚል ርዕስ የመጀመሪያ መድሐፉን አሳተመ። በወቅቱም ባቀረብነው ግምገማ መጽሀፉ ልብወለድ ቢሆንም ደራሲው
በአብዞኞቻችን ልብ ውስጥ የሚንሸራሽረውን ወይንም በህብረተሰባችን የዘር ግኑኝነትን አስመልክቶ በሀገራችን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሆነ ብሎ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም በፈጠረው ተንኮል ወገኖች እንዴት አስከፊ ችግር ውስጥ እንደወደቁ የሚገልጽ መሆኑን ነበር። ደራሲው በልብ ወለድ ስም በጣፈጠና በሚያስደስት አቀራረብ ታሪኩን ቁልጭ አድርጎ በማቅረቡ መጽሀፉን ላነበብነው ሁሉ የዘላለም ትምህርትና ግንዛቤ ሰጥቶን አልፎአል።

ይህ ሁለተኛው መጽሀፉ በመሠረተ ይዘቱ “ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ” ሲሆን ነገር ግን በአመዛኙ በቃል ሲነገርለት የኖረ በሀገራችን
የብሔራዊ የፖለቲካ አመራር ባህርይ ላይ ያተኮረ ነው። ዶክተር ጌታቸው መካሻ፤ በዓፄ ሀይለ ሥላሴ ዘመን የማስታወቂያ ሚኒስትር፤ የደራሲውም በዚያን ጊዜ አለቃ የነበሩ ለመጽሀፉ መግቢያ እንዲሆን በማሰብ የዓፄ ሀይለ ሥላሴ መንግሥት ለሀገሪቱ መሻሻልና ለአከናወኖአቸው የልማት ተግባራት መጠነኛ፣ ነገር ግን በቂ ማብራሪያ ለአንባብያን አቅርበዋል። የደራሲውን ችሎታ፣ ቅን ሠራተኝነት የሥነ ጽሁፍ ተሰጥኦ ምሥክርነታቸውን ለግሰዋል።

የሰው ልጅ የሶሻልና የፖለቲካ ግንኙነቶች ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አንዱ ባንዱ ላይ የበላይ ወይንም ገዥ፤ እንደዚሁም
ተጠቃሚ ለመሆን ተንኮልና፤ ሤራ በግሉም ሆነ በወል ሲፈጽም እንደኖረ የማይካድ ነው። በየትኛውም ሀገርና ጊዚያት የተከሰቱ
ማናቸውም መንግሥታት ወይም መሪዎች ከዚህ ዓይነቱ ተንኮልና ሤራ የጠሩ ናቸው ለማለትም ያስችግራል። የተንኮሉ ጭካኔ፤ ስፋቱና ጥልቀቱ በተገዥው ሕዝብ ላይ የሚያደርስው ጉዳትና መጠን ይለያይ እንጅ የእያንዳንዱ የፓለቲካ መሪ ተንኮልና ሤራ ለሕዝብ በይፋ በተገለጸ ቁጥር ሲያስገርመንና ሲያሳዝነን ኖሮአል።

የዓፄ ሀይለ ሥላሴ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአርባ ዓመታት በላይ ሲገዛና ሲያስተዳድር በአመዛኙ በሀይልና እንደዚሁም በወቅቱ በሚቻሉ ልዩ ልዩ የአስተዳደር ዘዴዎችና ተንኮሎች እየተጠቀመ በስርዐቱ ላይ ሊያሳምጹ የሚችሉ ሁኔታዎችን ይቆጣጠር እንደነበር በሰፊው የሚነገር ነው። መጽሀፉ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከጠላት ወረራ በህዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓፄ ሀይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት ውስጥ ስለተከሰተው የሥልጣን ሽኩቻ ሲሆን፤ ይኽውም በአንድ በኩል በተግባር ለንጉሱ ቀረቤታ በነበራቸው በፅሕፈት ሚኒስትሩ በፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስና በሌሎች የሚንስቴር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች በተለይም በገንዘብና በማስታወቂያ ሚንስትሩ በአቶ መኮንን ሀብተወልድ የተካሄደ ውዝግብ ነው። በተለይም ንጉሡ በፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ዋና ተዋናይነት በረቀቀ ስልት  አስተዳደር አስቸግሮአቸው የነበረውን የፊውዳል ስርዓት ለመደምሰስ መፈንቅለ መንግሥት እንዲደራጅ ማቀዳቸውና መፍቀዳቸው  በጣም የሚያስገርም ድርጊት ነው።

ከዚህ መጽሀፍ አንባቢያን የሚገነዘቡት ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ይኖራሉ፤ አንደኛው በኢትዮጵያ ታሪክ ምናልባትም በዓለም ደርጃ
ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ንጉሥ ከላይ እንደተጠቀሰው በራሳቸው አገዛዛ ላይ መፈንቅል እንዲደረግ መዶለታቸው ሲሆን፤ እንደዚሁም ከጣሊያን ወረራ በኋላ የተመሠረተው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መንግሥት የተለመደውን የመንግሥት ሥርዐት ያልተከተለ  እንደነበረና ይኸውም አንድ የጽሕፈት ሚኒስትር ለንጉሡ ቅርበት ስላለው ከመጠን በላይ ሀላፊነት በመሽከሙ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁሉ ሳይቀሩ በሚያስገርም ሁኔታ በዚሁ ሚንስቴር ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ መደረጉን እናያለን። በተጨማሪም ፀሀፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ  በአፈ ታሪክ እንደሰማነው ተንኮለኛ እንደነበሩ ሲሆን፣ የሚወራውና የሚተረከው ሁሉ ከእውነት የራቀ ለመሆኑ በየአጋጣሚው በሚወስዱዋቸው አቋሞችና በሚያስተላልፉዋቸው መመሪያዎች በዚሁ መጽሀፍ አማካኝነት ለማወቅ ተችሎአል።

“ሤራ፤ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት” አንደኛው ክፍል መጽሀፍ ሲሆን ሁለተኛውና ተከታታዩ በዝግጅት ላይ መሆኑን ደራሲው
ጠቁሞናል። መታተሙንም በጉጉት እንጠብቃለን።

በመጨረሻም አቶ ወርቅ አፈራሁ ከበደን የማሳስበው ቢኖር ከተቻለ መጽሀፉ በእንግሊዘኛ ተተርጉሞ የእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚቀናቸው ሁሉ እንዲያነቡት የሚደረግበት ዘዴ ቢፈለግ መልካም ይመስለኛል። በዚህ መልክ የተፃፈ መጽሀፍ በወጣቶች ለመነበብ ያለው ዕድል ከፍተኛ እንደሚሆን አልጠራጠርም።

መጽሀፉ 271 ገጾች ያዘለ ሲሆን የታሪኩ አፃፃፍ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ሰስፔንስ የተሞላበት፤ የሚቀጥለውን ተከታይ ሁኔታ ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት የሚፈጥር ስለሆነ፤ አንዴ ማንበብ ከተጀመረ ለማስቀመጥ ወይንም በይደር ለማስተላለፍ ይከብዳል።

የአቶ ወርቅ አፈራሁ ከበደ ሁለቱም ተከታታይ መጽሀፍቶች ጣእም ያላቸው በቀላሉ አንብቦ ለመረዳት በሚያስችሉ ቃላቶችና ዓረፍተ ነግሮች የተጻፉና ትምህርት አዘል ስለሆኑ ማንም ሰው ቢያነበው እንደሚረካ አምናለሁ።

መጽሐፉን ለመግዛት የምትፈልጉ ሁሉ workkebede@yahoo.com በሚል የኢሜል አድራሻ በመጻፍ ወይም
ስልክ ቁጥር 301-332-0245 በመደወል መጽሓፉን ማግኘት ትችላላችሁ።

የመጽሐፉ ዋጋ $20 የአሜሪካን ዶላር

ስለሺ ጥላሁን

ነሐሴ 30፣ 2001 ዓ ም

Monday, September 21, 2009